የዛሬ አስር ዓመት ገደማ ትንንሽ ስልኮችን በይክሳችን ይዘን ስንዞር እና ስናወራ፣ ስክሪናቸው የሚነኩ ስማርት ስልኮችን ሳንይዝ በፊት ሁለት ሜጋ ፒክስል ጥራት ያላቸው ሞባይል ስልኮች እንኳን ብርቅ በነበሩበት ጊዜ ምስሎችንና ዶክመንቶችን ከስልክ ላይ መላላክ እንዲሁም አጠገብ እንዳለ ሰው ቻት ማድረግ በዓለም ዙሪያ ካሉ ሰዎች ጋር ሁሉ በIM (Internet Messaging) እንደዚህ መቀራረብ እንደሚቻል የሚነግረን ሰው ቢኖር ለብዙዎች ለማመን ከባድ በሆነ ነበር::

ዓመታት በዓመታት ሲተኩና ቴክኖሎጂውም ከዘመናት ፍሰት ሁሉ በላቀ ፍሰት ሲመጥቅ ግን ትሩፋቶቹ ለኛም ተርፈው በቅድሚያ የሞባይል ኢንተርኔትን ከመጠቀም የጀመረው እድገት በተለይም የስማርት ስልኮች በከፍተኛ ሁኔታ ዋጋ መቀነሳቸውን እንዲሁም ትልልቅ የሞባይል አምራች ኩባንያዎች የአፍሪካን ገበያ አላማ አድርገው መንቀሳቀሳቸው በተጨማሪ ደግሞ Open Source የሆነው የአንድሮይድ መፈጠር የተጠቃሚዎችን ቁጥር በእጅጉ ሲጨምር አጠቃቀሙም እያደገ እንዲቀጥል አስችሎታል::

ቫይበር፣ ዋትስ አፕ፣ የፌስ ቡክ ሜሴንጀር፣ ጉግል ቶክ (አሁን ሀንግ አውት)፣ ኢሞ፣ ቴሌግራም በየራሳቸው የመጠቀሚያ መንገዶች በየወቅቱ ስንጠቀማቸው ቆይተናል:: አሁን ግን የሀገራችን ልጆች የራሳችንን ቋንቋዎች እና ለኢትዮጵያውያን በተዘጋጁ አቀራረቦች ሜዳ ቻት የተሰኘ መተግበሪያ አቅርበውልናል:: የሜዳ ቻት መስራችና ሥራ አስኪያጅ የሆነውን ብሩክ ኃይሉን ስለመተግበርያው ጠይቀን እናም ያወቅነውን እንደዚህ ይዘን መጥተናል:: ሜዳ ቻት ለእኛ ሀገር ተጠቃሚ ታስቦ የተሰራ እንደመሆኑ መጠን ሌሎቹ የመልክት መላላኪያ መተግበሪያዎች ከሚሰጧቸው አገልግሎቶች ለየት ባለ መልኩ ሶስት የሀገራችንን ቋንቋዎች ያካተተ ሲሆን በተለይ ደግሞ ከአሞሌ የሞባይል ክፍያ ስርዓት ጋር በመቀናጀት ብር ለመላላክ፣ የሞባይል ካርድ እና ሙዚቃዎች ለመግዛት እና ሌሎችንም እንደ ክፍያዎች ለመፈፀም እንዲያስችል ተደርጎ ተሰርቷል:

መተግበርያው በተለይም ደግሞ አሁን አሁን እጅግ አሳሳቢ የሆነውን የመረጃ መረብ ደህንነት መስተጓጎል ችግር እንዳያጋጥመው የሚላኩ መልዕክቶችን ከላኪውና ከተቀባዩ ሁለት ፅንፎች በሚኖሩ የተለያዩ የምስጢር ቁልፎች እንዲናበቡና በየትኛውም መካከል በሚገኝ ሰርቨር ላይ መከፈት እንዳይችል ተደርጎ የሚቆለፍ መሆኑ የታመነ እንዲሆን ያስችለዋል:: በተጨማሪም ስልክዎ ቢጠፋ ወይም ስልክ ቢቀይሩ መተግበሪያውን ድጋሚ በመጫንና ወደ መለያ አድራሻዎ ብቻ ሲገቡ መልዕክቶችዎ ሁሉ እንደነበሩ ስለሚያገኙአቸው የሚያሳስብዎ ነገር አይኖርም:: ሜዳ በአሁኑ ሰዓት ከአስራ አራት ሺህ በላይ ተጠቃሚዎችና ያፈራ ሲሆን በተለይ ደግሞ የመተግበርያው ተጠቃሚ ከሆኑ በሜዳ ጌም ላይ በመሳተፍና በቀጥታ የጠቅላላ እውቀት ጥያቄዎችን በመመለስ እስከ 10,000.00 (አስር ሺህ ብር) ድረስ ማሸነፍ ይችላሉ::

Source: Zur Selasa Digital Magazine