Categories: In the news

ውይይት በ‹‹ሜዳ ቻት››

በሻሂዳ ሁሴን

አቶ ብሩክ ኃይሉ የስሪ ሲክስቲ ግራውንድ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ስሪ ሲክስቲ ከተቋቋመ ዘጠኝ ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፣ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ የተለያዩ ሥራዎችን በኢትዮጵያ ውስጥና ከኢትዮጵያ ውጭ ለሚገኙ ተቋማት ሲሠራ ቆይቷል፡፡

በቀላል የዌብ ሳይት ዲዛይን ገበያውን የተቀላቀለው ድርጅቱ፣ ውስብስብ የሆኑ ለባንኮችና ለተለያዩ ፋይናንስ ተቋማት የሚውሉ የቴክኖሎጂ ሥራዎችንም ይሠራል፡፡ ፈረንሣይ፣ ዩናይትድ ኪንግደምና አሜሪካ ከሚገኙ የውጭ ድርጅቶች አብረው ሲሠሩ፤ የአገር ውስጥ ድርጅቶች የሚከፍሏቸውን ሦስት አጥፍ ያህል እንደሚያገኙ ይናገራሉ፡፡

‹‹የእኛ አገር ደንበኞች እንዲሠራላቸው የሚጠይቁት ነገር ብዙ ጊዜ የተሟላ አይሆንም፡፡ አንድ ነገር እንድንሠራላቸው ጠይቀውን እየሠራን ሳለ በመሀል ተነስተው ሐሳብ ይቀይራሉ፡፡ ይኼ በጣም ጊዜና ጉልበት ያባክናል፤›› የሚሉት አቶ ብሩክ፣ የውጭ ድርጅቶች የሚከፍሉት ገንዘብ ከፍተኛ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን የሚያቀርቡላቸው የሥራ ውሎች የተሟሉ በመሆናቸው አብሮ ለመሥራት እንደማይቸገሩ ይናገራሉ፡፡

ቴክኖሎጂ በጂኦግራፊ አይወሰንም የሚሉት አቶ ብሩክ፣ ሥሩ የተባሉትን ለመሥራት አሜሪካ ሄዶ መጫረት ሳያስፈልጋቸው ባሉበት ሆነው ፕሮጀክቶችን ወስደው እንደሚሠሩ ይገልጻሉ፡፡ በብዙ መልኩ ከምዕራባውያን ዕርዳታ ከምትጠብቀው ኢትዮጵያ ብቁ አገልግሎት እንሰጣለን የሚሉ እንደ ስሪሲ ክስቲ ያሉ ድርጅቶችን የመጠራጠር ነገር ቢኖርም፣ ከዚህ ቀደም አብረዋቸው የሠሩ አካላት በአገልግሎታቸው መደሰታቸውን ከገለጹ ሥራውን ይወስዳሉ፡፡ የተዋዋሉትን ገንዘብ የሚያገኙትም ጥርት ያለ ሥራ ሠርተው ሲያስረክቡ ብቻ ነው፡፡ በፈረንሣይ፣ በአሜሪካና በዩናይትድ ኪንግደም ከሚገኙ ድርጅቶች ጋር የሠሯቸው ሥራዎች የኢኮሜርስ (የኢንተርኔት ግብይት) ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡

ከዘመን ባንክ፣ ዳሸን ባንክ፣ ከአግሪካልቸራል ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲና ከሌሎችም በርካታ ድርጅቶች ጋር አብረው እንደሠሩ ይናገራሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ለየድርጅቱ የሚሠሯቸውን ሥራዎች አቁመው ትኩረታቸውን በአንድ ጉዳይ ላይ አድርገዋል፡፡ በሞባይል መልዕክትና ገንዘብ መላላክ በሚያስችለው ‹‹ሜዳ ቻት›› በተሰኘ ፕሮጀክታቸው ላይ ትኩረት አድርገው መሥራትን መርጠዋል፡፡ ሜዳ ቻት በሞባይል ስልክ ላይ መልዕክት መላላክ ገንዘብ መቀባበል የሚያስችል በኢትዮጵያ ልጆች የተሠራ አዲስ ቴክኖሎጂ ነው፡፡

ሜዳ ቻት እንደ ፌስቡክ ማኅበራዊ ሚዲያ ሳይሆን፣ ሁለት ሰዎች ግላዊ መልዕክት የሚላላኩበት አውታር ነው፡፡ ሰብሰብ ብለው ማውራት ለሚፈልጉም እንደ ዋትስአፕ በቡድን መልዕክት መላላክ የሚችሉበት ጥግ አለው፡፡ ዕለታዊ ዜናዎች፣ ገበያና ሌሎችንም አገልግሎቶች ማግኘት የሚያስችሉ ቻናሎችም አሉት፡፡ በኢንተርኔት ኮኔክሽን በሚሠራው ሜዳ ቻት የጽሑፍ መልዕክት፣ ፎቶ፣ ቪዲዮ መላላክ ይቻላል፡፡

ከሁሉ ነገር በላይ ደግሞ ለቸገረው ባልንጀራዎ ወይም ዩኒቨርሲቲ ለምትማር ልጅዎ የትም መሄድ ሳያስፈልግዎት ገንዘብ መላክ ያስችሎታል፡፡ ሜዳ ቻት የገንዘብ ዝውውሩን የሚያቀላጥፈው የዳሸን ባንክ አገልግሎት በሆነው አሞሌ ሞባይል ባንኪንግ በኩል ነው፡፡ በሜዳ ቻት ገንዘብ መላላክ የሚፈልጉ ከሆነ ወደ አንዱ የዳሸን ባንክ ቅርንጫፍ ጎራ ብሎ አሞሌ ሞባይል ዋሌት ክፈቱልኝ ብሎ የስልክ ቁጥር መስጠት ነው፡፡ አሞሌ የክፍያ ሥርዓት ከሜዳ ቻት በጋራ ስለሚሠራ በቀላሉ ገንዘብ መላክ ይችላሉ፡፡ የሚልኩለት ሰው ገንዘቡን ለማግኘት የግድ የሜዳ ቻት ተጠቃሚ መሆን አይጠበቅበትም፡፡

ገንዘብ መላላክ ብቻ ሳይሆን በሜዳ ቻት የተለያዩ ግብዓቶችንም መፈጸም ይቻላል፡፡ ስልክን ጨምሮ ሌሎች የተለያዩ ኤልክትሮኒክሶችና ልዩ ልዩ መገልገያዎችን መሸጥ መግዛት ይችላሉ፡፡ የሲኒማ ቤት ትኬቶች፣ የተለያዩ ዝግጅቶች መግቢያ ካርዶች ከሜዳ ቻት የግብይት መስኮት መግዛት ቀላል ነው፡፡

‹‹ኩሩ ነው ሕዝባችን ዳር ድንበሩን ያስከበረ፡፡ በታሪካችን አልተወረርንም፡፡ ነገር ግን የምንጠቀማቸው ቴክኖሎጂዎች በሞላ የውጭ ናቸው፡፡ ቴክኖሎጂዎቹም በሌላ ሰው ቋንቋና እይታ የተሠሩ ናቸው፡፡ በተዘዋዋሪ መንገድ ቅኝ የመገዛት ነገር ፈጥሯል፤›› የሚሉት አቶ ብሩክ፣ ሜዳ ቻት ኢትዮጵያዊ እሴትና ባህል እንዲያንፀባርቅ ተደርጎ መዘጋጀቱን ይገልጻሉ፡፡

አማርኛ፣ ኦሮሚኛ፣ ትግርኛ ቋንቋዎችን ተጠቅመው መልዕክት መላላክ ይችላሉ፡፡ በቅርቡም ሌሎች ቋንቋዎችን ለመጨመር እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ስሜትን መግለጽ የሚችሉ ምሥሎች (ስቲከሮች) ኢትዮጵያዊ ለዛ ኖሯቸው ተዘጋጅተዋል፡፡ ገንዘብ የላኩለት ሰው ጠይም ቆዳ ያለው ፀጉሩን ያቆመ በአንድ ዓይኑ የሚጣቀስና ይመችህ የሚል የአራዳ ልጅ ስቲከር ይልክሎታል፡፡

ይመችህ የሚለውን ቀጭኑን ልጅ ሰፈርዎ፣ መሥሪያ ቤት፣ ታክሲ ላይ ብቻ የሆነ ቦታ ያውቁታል፡፡ ይመችህ ሲሎት ደግሞ በተደረገለት ነገር ተደስቶ ማመስገኑ እንደሆነ እንኳን እርሶ ፊደል ያልቆጠሩም ያውቁታል፡፡ ያሰቡትን በአፍ መፍቻ ቋንቋዎች እንደ ልብ መግለጽ እንዲችሉ የተዘጋጀ ነው፡፡ ትርጉማቸውን በማይረዱት የነጮች ስቲከር አይደናበሩም፡፡ ከጻፉት አጭር መልዕክት በኋላ በሚያውቁት ለዛ ስሜቶን የሚገልጽ ስቲከር መላክ ይችላሉ፡፡ የፈለጉም በእንግሊዝኛ ማውራት የሚችሉትን የላቲን ፊደልም ተካቷል፡፡ በቅርቡም የሌሎች ማኅበረሰብ ቋንቋዎች እንዲሁም እንደ ሁለተኛ ዜጋ መቆጠር የጀመሩት ቻይናዎች መግባቢያ ማንደሪን ቋንቋን በሜዳ ቻት ማቀላጠፉ ታውቋል፡፡

የእንግሊዝን አፍ መናገር ወይም A B C D መቁጠር ሳያስፈልግ በሚያውቁት የግዕዝ ፊደል መልዕክቶችን ይላላካሉ፡፡

ይህም ሜዳ ቻት በዕድሜ ሳይገደብ ሁሉም ዓይነት የኅብረተሰብ ክፍል እንዲጠቀመው መንገድ ከፍቷል፡፡ አቶ ብሩክና ግብረ አበሮቻቸው የነበራቸው ግምት በአብዛኛው ወጣቱ የኅብረተሰብ ክፍል ይጠቀመዋል የሚል ቢሆንም፣ አዋቂዎችና አዛውንቶች ጭምር የሜዳ ደንበኛ መሆናቸው አስደስቷቸዋል፡፡

ሜዳ ቻትን በየትኛውም የዓለም ጥግ የሚገኙ እንዲጠቀሙት በጂኦግራፊ ሳይገደብ ተዘጋጅቷል፡፡ አፕሊኬሽኑን በስልካቸው ጭነው በመገልገል ላይ ከሚገኙ ደንበኞቻቸው መካከል እስከ 15 በመቶ የሚሆኑት ዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ አብዛኞቹም ዓረብ አገር የሚገኙ እንደሆኑ አቶ ብሩክ ተናግረዋል፡፡ ባንክ ቤት ሄዶ ወረፋ መጠበቅ ሳያስፈልግ፣ የሞባይል ቁልፎችን ተጭነው ገንዘብ መላክ ይችላሉ፡፡ የሜዳ ቻት ተጠቃሚ ላልሆኑ ሰዎች ጭምር ገንዘብ ይላካል፡፡

ለአገራዊ ባህልና እሴት ትልቁ ቦታ የሰጠው ሜዳ ቻት ከአምስት ወራት በፊት ነው ሰፊው ሕዝብ እንዲገለገልበት ገበያ ላይ የዋለው፡፡ እስካሁንም 22 ሺሕ ደንበኞች አፍርቷል፡፡ ለሕዝብ ይፋ በተደረገ በሦስት ወራት ውስጥም ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ በሜዳ ቻት መንሸራሸሩን አቶ ብሩክ ይናገራሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት 14 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን የስማርት ስልክ ተጠቃሚ ናቸው፡፡ ይህ ቁጥር ከአምስት ዓመታት በኋላ 40 ሚሊዮን ይደርሳል ተብሎ ይገመታል፡፡ ስሪሲክስቲም ከአምስት ዓመታት በኋላ 40 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ሜዳ ቻት እንዲጠቀሙ ለማድረግ የረዥም ጊዜ ዕቅድ ይዟል፡፡

የሜዳን ፕሮጀክት ዕውን ለማድረግ ለቴክኖሎጂ ልዩ ፍቅርና ተሰጥኦ ያላቸው እንደ አቶ ብሩክ ያሉ ሌሎች ወጣቶች አምስት ዓመታት ያህል ለፍተዋል፡፡ አሁን ያለበትን ይዘት እንዲያገኝ ብዙ ጥረዋል፡፡ የማይታለፉ የሚመስሉ ፈተናዎችን አልፈዋል፡፡ ሙሉ ወጪውን የሸፈኑትም ከራሳቸው እንደሆነ አቶ ብሩክ ይናገራሉ፡፡ ከዚህ በኋላ ያለውን ግን አቅሙ ካላቸው ሰዎች ጋር አብሮ ለመሥራት ኢንቨስተሮችን ማነጋገር ጀምረዋል፡፡

ዓመታት የፈጀባቸውንና ብዙ መዋዕለ ንዋይ ያፈሰሱበት ፕሮጀክት እንዴት ተጠቃሚ ሊያደርጋቸው ይችላል የሚል ጥያቄ ማጫሩ አይቀርም፡፡ ስሪ ሲክስቲም በዚህ ረገድ የተዘጋጀበትና ትርፋማ ሊያደርገው የሚችል የአሠራር ቀመር አለው፡፡ ድርጅቱ ገንዘብ የሚሰበስበው ከመደበኛ ደንበኞቹ አይደለም፡፡

ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመሆን የሞባይል ካርድ ይሸጣሉ፡፡ ካርዱን ሸጠው የሚገኘውን ትርፍ የድርጅቱ ገቢ ይሆናል፡፡ የኮንሰርት ትኬትም ይሻሻጥበታል፡፡ የደንበኞች ቁጥር እየጨመረ ሲሄድም የማስታወቂያ ገበያንም ይስባል፡፡ ለተመረጡ የኅብረተሰቡ ክፍሎች እንዲደርሱ የሚፈልጉ ማስታወቂያዎችን መላክ የሚፈልጉም ለሥሪ ሲኪስቲ ገንዘብ እየከፈሉ ሜዳ ቻችን ሊጠቀሙበት ይችላሉ፡፡

Selamawit

Share
Published by
Selamawit

Recent Posts

ሜዳ ኮድን እንዴት አሳደግነው?

ኪው.አር ኮድ QR CODE እ.ኤ.አ በ1994 ዓ.ም በጃፓን የተፈጠረ የሁለት ልኬት (two dimensional) የሆነ የባር…

1 year ago

ICT Expo Ethiopia 2019

ICT Expo Ethiopia 2019 opened on 6 June 2019 At the Millennium Hall. Deputy Prime…

2 years ago

Meda Chat team on Fana TV

https://www.youtube.com/watch?v=rtgJbWfJOCI&feature=share

2 years ago

Meda Chat on Kana TV #Shikela

ከቃና ቴሌቪዥን ጋር ስለሜዳ ቻት ያደረግነውን ቆይታ ይመልከቱ #ሜዳቻት #የሜዳክፍያ #ሽቀላ https://www.youtube.com/watch?v=Qoq9ZfGaPZU&amp

2 years ago

AAES Horse Jumping Competition

[gallery type="rectangular" ids="73190,73189,73192,73191"]

2 years ago

ከ አዲስ ቲቪ ሳይ ቴክ ፕሮግራም ጋር ያደረገነው ቆይታ

https://www.youtube.com/watch?v=CTk-gl31MTQ Source: Addis TV

2 years ago